መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ባያወጣ ይሻለው ነበር...

መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ባያወጣ ይሻለው ነበር። አሊያም ታወጀ ስለተባለው "ኮማንድ ፖስት" አጠር ያለ መረጃ መስጠት ይሻል ነበር። ከዛ ውጭ የተሰጠው መግለጫ ግን ከአንድ የሀገር ፀጥታ ኃይል የማይጠበቅ፣ በፀረ ትህነግ ዘመቻው የኢትዮጵያ ሕዝብ "ከጎንህ ነን" ካለው አካል ፈፅሞ የማይጠበው ነው።
1) በመተማ መስመር የተፈፀመውን በቅማንትና በአማራ ሕዝብ መካከል ተፈጥሮ የነበረ አስመስሎ ማቅረብ ፈፅሞ ስህተት ነው። ይህ ቡድን የሕዝብን አላማ የያዘ ቡድን አይደለም። የትህነግን፣ ከዛም አለፍ ሲል የሱዳንና ግብፅን አላማ ይዞ እየተላላከ ያለ ፀረ ሀገረ መንግስት ቡድን ነው። ሀገር የካደ ተብሎ በይፋ መጠራት ያለበት ቡድን ነው። ይህ ቡድን በቅርቡ ጥቃት የፈፀመው በአማራ ልዩ ኃይልና በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ነው። ትህነግ በመከላከያ ሰራዊቱና በአማራ ልዩ ኃይል ጥቃት ሲፈፅምኮ "በትግራይና በአማራ/በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል" ተብሎ አልተገለፀም። መገለፅም አልነበረበትም። በቅማንት ሕዝብ ስም የሚያወናብደው ቡድን የግብፅን ባንዲራ ይዞ ሲንቀሳቀስ የፀጥታ ኃይሉም ታዝቧል። ይህ ኃይል በመከላከያ ሰራዊትና በአማራ ልዩ ኃይል ላይ የፈፀመውን አብሮ የኖረ ሕዝብን ግጭት/ ግጭት ለማስመሰል የተደረገ አስመስሎ ማቅረብ ትክክል አይደለም።
በመከላከያ ሰራዊትና በአማራ ልዩ ኀይል ላይ ጥቃት የፈፀመ አካል በቅርቡ የሚዲያ ዘመቻ ያደርጋል። የሚዲያ ዘመቻው ማጠንጠኛ በቅማንት ሕዝብ ላይ ጥቃት እንደደረሰ በማስመሰል ነው። የዛሬው የመከላከያ መግለጫ ለዚህ ቡድን አጋዥ ነው። ሀገርን የካደ ቡድንን ጉዳይ ከሕዝብ አስመስሎ ማቅረብ ለዚህ ሀገር ከሃዲ ቡድን እገዛ ነው። ከመከላከያ ሰራዊቱ እንዴት መሰል መግለጫ ይሰጣል?
2) በተመሳሳይ በወለጋና አጣዬ እጅግ የተደራጀ ኃይል በንፁሃን ላይ ያደረሰውን ጥቃት ሕዝብ ለሕዝብ ለማጋጨት የተደረገ አስመስሎ ማድበስበስ ለሕዝብ ቀድሞ ደርሶ ጥቃት ማቆም ከነበረበት፣ ወንጀለኛን ወንጀለኛ ብሎ መጥራት ከነበረበት አካል ፈፅሞ የሚጠበቅ አይደለም። ከተማ እያወደመ የተስፋፋን ኀይል በዚህ መጠን ማድበስበስ ሕግ ለማስከበር ያለው ቁርጠኝነት ምን ያህል ደካማ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ጥቃት ፈፃሚውን በሚገባው ስም መጥራት ያልቻለ፣ ቢያንስ አላማውን ያዛባ አካል በምን መልኩ ሕግ ያስከብራል?
3) እጅግ የሚገርመው የመከላከያ ሚኒስቴር አወጣው በተባለ መግለጫ ከተሰጡት ማሳሰቢያዎች መካከል "በጋራም ሆነ በተናጠል ቤተ ክርስትያን፣ ቤት ማቃጠል፣ ማውደም የተከለከለ ነው።" አይነት ሀሳብ ይዟል። እንዴ? ምን አይነት መግለጫ ነው። ይህኮ ወንጀል እንጅ በኮማንድ ፖስት የሚከለከል አይደለም። መሰል ችግር ሲፈጠር "ክልክል ነው" የሚባለው ቤት ማቃጠል አይደለም። በመሰል ሁኔታ ላይ "ስብሰባ ማድረግ፣ ከምሽት ምናምን በኋላ መንቀሳቀስ፣ ከዚህ ቁጥል በላይ መሰብሰብ… ……" አይነት ነገር ነው የተከለከለ ተብሎ መግለጫ የሚሰጥበት። ቤት ማቃጠልማ ኮማንድ ፖስት ስለታወጀ አይከለከልም ድሮም ወንጀል ነው። ወንጀል ደግሞ የተከለከለ ነው ተብሎ መግለጫ አይሰጥበትም። መጀመርያ መብት የነበረ ያልተከለከለ ነገር ነው፣ በአዲስ ሁኔታ "የተከለከለ ነው።" የሚባለው።
4) ስለ ደረሰው ጥቃትም ማዘንና መፅናናትን ከመከላከያ አንጠብቅም። "ወንጀለኞችን ከገቡበት ገብተን ይዘን ለፍርድ እናቀርባለን" እንዲል ነው የምንጠብቀው።
መከላከያ ሚኒስቴር በሆነ አጀንዳ "ኧረ ቶሎ በሉ" ተብሎ መግለጫ ከሚሰጥ ቢቀር ይሻል ነበር። አሊያም ስለ "ኮማንድ ፖስቱ" አጠር ያለ መረጃ መስጠት ይቻል ነበር። መግለጫ "አቋም" ነው። ሀገር የካደን ኃይል ሕዝብ ለሕዝብ ያጋጨ አድርጎ አቋም መያዝ ትክክል አይደለም። በወለጋና በአጣዬ ያየነውም ከባድ መሳርያ የታጠቀ ኃይል ነው። ይህን አጥፊና አሸባሪ ኃይል ላይ በድርጊቱ ልክ ነው አቋም መያዝ ያለበት እንጅ አሸባሪዎቹ ፖለቲካ ለመስራት ሕዝብን ተጠልለው የሚሰሩትን ፖለቲካ የሚያግዝ አቋም ማንፀባረቅ በፍፁም ስህተት ነው።
"ቤተ ክርስትያንና ቤት ማቃጠል፣ ማውደም የተከለከለ ነው።" የሚል መግለጫ በምንም ተአምር ከመሰል ተቋም የሚጠበቅ አይደለም።
 
From Getachew Shiferaw